ባራክ ኦባማ በኢልሃን ኦማር ላይ የተከፈተውን የወንጀል ምርመራ "እጅግ አስቀያሚ" ሲሉ አወገዙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር በአሜሪካ ፌደራል መንግሥት የወንጀል ምርመራ የተከፈተባት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አጥብቃ ስለምትተች ነው ሲሉ ባራክ ኦባማ ተናገሩ።

"የፌደራል መንግሥቱ ሙሉ አቅሙን እየተጠቀመ ያለው ሕግ አክባሪ እና በሕዝብ የተመረጠች ባለሥልጣን ላይ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ፕሬዝዳንቱን ለመተቸት መድፈሯ ነው" ብለዋል።

በኢልሃን ኦማር ላይ የተከፈተውን ምርመራ "በጣም አስቀያሚ" ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባማ ኮንነዋል።

ዋይት ሀውስ እንዳለው በምክር ቤት አባሏ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የከፈተው ምርመራ "ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር" ያለመ ነው።

ባለፈው ሳምንት የአገር ውስጥ ደኅንነት ባልደረቦች በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የኢልሃን መኖሪያ ቤት ፈትሸዋል።

የሚኒሶታዋ የዴሞክራት ፓርቲ የምክር ቤት ተወካይ ወደ አሜሪካ በስደት የገባችበት ሒደት ላይ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል። ፍተሻውም ከዚህ ምርመራ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

ሶማሊያ የተወለደችው ኢልሃን ወደ አሜሪካ ከቤተሰቦቿ ጋር የተጓዘችው በልጅነቷ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1995 አሜሪካ ስትገባ ዕድሜዋን ዋሽታ ሊሆን ይችላል በሚል ምርመራ እየተደረገባት ይገኛል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኦባማ በኤክስ ገጻቸው እንደጻፉት፤ የኢልሃን አባት የአሜሪካ ዜጋ የሆኑት ኢልሃን 17 ዓመት ሳይሞላት በፊት ስለሆነ አሜሪካዊ የመሆን መብት አላት።

"ይሄ አስተዳደር የምክር ቤት አባሏን ከአገር ለማባረር እየሞከረ ነው። አባቷ የአሜሪካ ዜጋ የሆኑት እሷ 18 ዓመት ሲሞላት ስለሆነ ዜግነት የማግኘት መብት የላትም የሚል ተጨባጭ እውነታ የሌለው መላ ምት አቅርበዋል" ሲሉም ተችተዋል።

"እንዲህ ያለ አካሄድ ከተለመደ እሷ ላይ ብቻ አይቆምም። ከሁለቱም ፓርቲዎች የሚመረጡ ቀጣይ ፕሬዝዳንቶችም ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ" ሲሉም አክለዋል።

በአሜሪካ የዜግነት ሕግ መሠረት ከአገሪቱ ውጭ የተወለዱ ሰዎች 18 ዓመት ሳይሞላቸው በፊት ከወላጆቻቸው አንዳቸው የአሜሪካን ዜግነት ካገኙ ዜጋ የመሆን መብት አላቸው።

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሎውረን ቢስ ምርመራው ፖለቲካዊ ዓላማ አለው መባሉን አስተባብለዋል።

"ጆ ባይደን እንዳደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱን እንደ መሣሪያ አይጠቀሙም። ዓላማው ሕግ እና ሥርዓትን ማስከበር ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ በድጋሚ ለመመረጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በፌደራል መንግሥቱ የተከፈተባቸው የወንጀል ምርመራ ፖለቲካዊ ዓላማ አለው ብለው ሲከስሱ ነበር።

የፍትሕ ሚኒስቴር ምርመራ ኢልሃን ዜግነቷን እንድትነጠቅ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ግን ሐሰተኛ መረጃ መቅረቡ መረጋገጥ ይኖርበታል።

በአውሮፓውያኑ 2023 እስራኤልን በተመለከተ በሰጠችው አስተያየት ምክንያት ከአሜሪካ ምክር ቤት ቁልፍ የኮሚቴ አባልነት ተባርራለች።

ትራምፕ ለዓመታት "መሠረት አልባ በሆኑ ውሸቶች እና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች" ዒላማ ሲያደርጓት እንደቆዩ ኢልሃን በተደጋጋሚ ተናግራለች።

የተከፈተውን ምርመራ በፕሬዝዳንቱ "ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር የሚደረገው ጥረት" አካል መሆኑን ተናግራለች።

ትራምፕ ምርመራው ከእሳቸው ጋር እንደማይገናኝ ገልጸው ኢልሃንን "የምታማርር መጥፎ ሰው" ብለዋል።

የኢልሃን ቤት ሲፈተሽ ስልኳ፣ ኮምፒውተሯ፣ ማስታወሻ ደብተሯ እና ፓስፖርቷ እንደተወሰደ የገለጹት ጠበቆቿ ንብረቶቿ እንዲመለሱ አሳስበዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው ፍተሻው ከመካሄዱ በፊት ለምክር ቤት አባሏ መረጃ አልተሰጣትም።